Address
Beside Flamingo Restaurant , Addis Ababa, Ethiopia.
Email
cetuethio@gmail.com
Phone
+251 11-5-1-54-37 +25111-5-15-79-97
Home » news  »  ኢሠማኮ 55ኛውን የጠቅላይ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ አካሄደ
ኢሠማኮ 55ኛውን የጠቅላይ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ አካሄደ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም የኮንፌዴሬሽኑን 55ኛ የጠቅላይ ምክር ቤት ስብሰባ 11ኛ ፎቅ በሚገኘው የኮንፌዴሬሽኑ የስብሰባ አዳራሽ አካሄደ፡፡የኮንፌዴሬሽኑን የ2017 በጀት ዓመት የእቅድ ሪፖርት ያቀረቡት የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ኢሠማኮ የተቋቋመበትን ዋና ዓላማ ለማሳካትና የሠራተኛውን መብትና ጥቅም ለማስከበር ሠራተኛውን በማህበር ማደራጀት ተቀዳሚ ተግባሩ በመሆኑ፤ የማደራጀት ምጣኔን ለማሳደግ 250 የመ/ሠራተኛ ማህበራትን ለማደራጀት ታቅዶ ከእቅዱ በላይ 274 አዳዲስ ማህበራት መደራጀታቸውን እና የአባል ሠራተኞችን ቁጥር ለማሳደግ በተያዘው እቅድ በ2017 ዓ.ም ብቻ 84,344 ሠራተኞች መደራጀታቸውን ገልጸዋል፡፡ በአሠሪና ሠራተኛ መካከል የሚፈጠሩ የስራ ላይ ግጭቶችን ለመፍታት በተከናወኑ ተግባራት 257 ግጭቶች በማህበራዊ ምክክሮሽ ሲፈቱ፣ ፍርድ ቤት ከቀረቡ 132 ፋይሎች 64ቱ ላይ ውሳኔ የተሰጠ ሲሆን ከነዚህም መካከል 43ቱ ለሠራተኛው የተወሰኑ መሆናቸውን በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡ የህብረት ድርድር ለማድረግና ለመደራጀት የማይፈቅዱ አሠሪዎችን በተመለከተ የቀረቡ ቅሬታዎችን፣ ከሠራተኛው የደመወዝ፣የጥቅማጥቅም፣ መብት ጥሰትና የሥራ ስንብት በተመለከተ የቀረቡ ቅሬታዎችን፣ የሙያ ደህንነትና ጤንነትን በተመለከተ የቀረቡ ቅሬታዎችን በመፍታትና ሌሎችንም ከሠራተኛው መብት ማስጠበቅ ጋር የተያያዙ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸው በስትራቴጂክ ዕቅዱ መሰረት ሲለካ አጠቃላይ አፈጻጸሙ 95% ይደርሳል ብለዋል፡፡ በዚህ በጀት ዓመት ልዩ ትኩረት በመስጠት በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ መሰረት የደመወዝ ወለል የሚወስን ቦርድ እንዲቋቋምና መጠኑ እንዲወሰን በተለመደው መልኩ ልዩ ልዩ አማራጮችን በመጠቀም ሎቢ በማድረግ ያልተቋረጠ የሚዲያ ዘመቻ እናደርጋለንም ብለዋል፡፡ የምክር ቤቱ አባላት ባነሱት ሀሳብ ሠራተኛውን በሚመለከት በመንግስት የሚወጡ ህጎችና ደንቦች ተገቢነት ላይ ከመሞገት አንጻር አቶ ካሳሁንን ማመስገን ይገባል ያሉት አንድ የም/ቤት አባል ሪፖርቱ አጠቃላይ ከሚሆን እያንዳንዱ ዘርፍ ምን ሠራ? ምን አልሰራም? በሚል ቢቀመጥ የተሻለ ይሆን ነበር ብለዋል፡፡ ሌላው የም/ቤት አባል ማህበራትን ለማደራጀት መንግስት ከኛ ጋር አቅዶ እየሰራበት መሆኑ ትልቅ እመርታ ነው ነገር ግን የግብር ቅነሳ ላይ ብዙ ጥረት ቢደረግም የፀደቀው ከተጠየቀው በታች በመሆኑ አሁንም በምግብ ነክ ምርቶች ላይ የተጣለው ታክስ እንዲቀነስ ጥያቄ ብናቀርብ ጥሩ ነው ብለዋል፡፡ አንዳንድ ምርቶች ወደ ክልሎች ሲሄዱ የሚጠየቁት የኮቴ ክፍያ ቁጥጥር እንዲደረግበት የቀረበው ጥያቄ መፍትሄ ባለማግኘቱ ህዝቡ ላይ የዋጋ ንረት እያስከተለ ስለሆነ እንደገና እንዲታይ ለሚመለከተው አካል ጥያቄ ማቅረብ ይገባል ያሉት ሌላው የም/ቤት አባል በሥራና ክህሎት ሚ/ር እየተዘጋጀ ያለው የሥራ ላይ ክርክሮች የሚፈቱበት ማንዋል ላይ ቶሎ አስተያየት ሰጥተን ሥራ ላይ እንዲውል ብናመቻች የሚል ሀሳብ አንስተዋል፡፡ ኢሠማኮ ራሱን የቻለ የስፖርት ክፍል እና የራሱ የስፖርት ክለብ ቢኖረው እንዲሁም ራሱን የቻለ ሚዲያ ቢኖረው ወይም ከሚዲያዎች አየር ሰዓት በመግዛት ለሠራተኛው መብት እያደረገ ስላለው ትግል መረጃዎችን ለሠራተኛው ቢያሰራጭ እንዲሁም የህግ አገልግሎት ወሳኝ በመሆኑ መዋቅሩንና ደሞዙን አሻሽሎ ራሱን የቻለ የህግ አገልግሎት ክፍል ሊኖረው ይገባል፤ የሚሉና ሌሎችንም ሃሳቦች ከም/ቤት አባላቱ የተነሱ ሲሆን ከመድረኩ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በመጨረሻም ምክር ቤቱ የ2017 ዓ.ም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሥራ ክንውን ሪፖርትን በሙሉ ድምጽ አጽደቆ በቀጣይ በአጀንዳነት በተያዘው የ2018 ዓ.ም የሥራና የበጀት ዕቅድ ላይ ውይይት አድርጎ በሙሉ ድምፅ አጽድቋል፡፡ በም/ቤቱ የተነሱ ሃሳቦችንና የተሰጡ ምላሾችን በቴሌግራም ገጻችን በሚታተመው የሠራተኛው ድምፅ ጋዜጣ ይዘን የምንመጣ ይሆናል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *